top of page
Search

የ 70% ህዝቦቿን የታሪክ ትውስታ የደመሰሰች ሀገር ። የታሪክ ትምህርት ካሪኩለማችን ስር-ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል!የ 70% ህዝቦቿን የታሪክ ትውስታ የደመሰሰ

የ 70% ህዝቦቿን የታሪክ ትውስታ የደመሰሰች ሀገር ። የታሪክ ትምህርት ካሪኩለማችን ስር-ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል! ጥቁር አሜሪካኖችን enslave ለማድረግ ከታሪካቸው መነጠል አስፈላጊ ነበር። ታሪኩን የሚያውቅ ህዝብ ጠንካራ የስነልቦና መሰረት ስለሚኖረው ለመግዛት አይመችም። አንዳንድ ነገሮችን አርቀው የማያስተውሉ ሰዎች ታሪክ፣ እና ትርክት ምን ያደርጋል፣ አሁን ያረረብንን እንጀራ ማብሰሉ ላይ ብናተኩር ይመረጣል ሲሉ ይደመጣሉ። እነዚ ታሪክ ስነልቦናን እንደሚያርቅ፣ ተግባር እና ባህሪን እንደሚገራ፣ የአሸናፊነት/ተሸናፊነትን ስንቅ እንደሚሰጥ ያልገባቸው ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ የረጅም ርቀት ሯጭ በሌሊት ተነስቶ የሩጫ ልምምዱን ሲጀምር፣ ከኢትዮጵያውያን በዘርፉ ለረጅም ግዜ የማሸነፍ ታሪክ የተቀዳ የአሸናፊነት ስነልቦናን ሰንቆ ነው። በዚህም ምክንያት ገና ሳይወዳደር በታሪክ እውቀቱ ላይ በተመሰረተው የማሸነፍ ስነልቦናው ምክንያት ብቻ የማሸነፉን ስራ 50% ሰርቶታታል። የእግር ኳስ ቡድናችን በአንጻሩ በዘርፉ ካለው ከክሽፈት ታሪካችን ጋር በተያያዘ፣ ሲለማመድም ይሁን ወደሜዳ ሲገባ የሽንፈት ስነልቦናን ሰንቆ ሲሆን ይሄ ከሌሎች ም ክንያቶች ጋር ተጨማምሮ ለውጤት አልባነታችን ጉልህ አስተዋእጾ አድጎዋል ተብሎ ይታመናል። በዚ ቀላል ምሳሌ እንዳስረዳሁት ታሪክ ስነልቦናን ይቀርጻል፣ ስነልቦና ደግሞ የምናደርጋቸውን ድርጊቶች ውጤታማነት ይወስናል። ከዛ በዘለለ ታሪክ መማሪያም ነው፣ ታሪክ ዝክር ነው፣ ታሪክ የአንድ ማህበረሰብ እንደ nation ያለው consciousness መሰረት ነው። የራሱ ታሪክ እውቀት የሌለው ማህበረሰብ ፣ በእርግጠኝነት በጊዜ ሂደት እንደ ማህበረሰብ ይከስማል። ብሄሮች የራሳቸውን ባህል፣ እና ቋንቋ ለማስጠበቅ ለጥናት እና ምርምር ከሚመድቡት በጀት ውስጥ ወጥ የሆነ የራሳቸውን ታሪክ ለማዘጋጀት በቂ በጀት መመደብ አለባቸው። የፌደራል መንግስቱም በዚ ዙሪያ በቂ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል። በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው ካሪኩለምም የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች (ኦሮሚያን ጨምሮ) በምኒሊክ ወደ ኢትዮጵያ ከመቀላቀላቸው በፊት የነበራቸው ታሪክ በቂ ቦታ ተሰጥቶት ሊካተትበት ይገባል። የአቢሲኒያ ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው ብሎ የማይረባ፣ ርካሽ ማምታቻ ውስጥ መግባት ተቀባይነት የለውም። ኢትዮጵያ ውስጥ የአንዱን ታሪክ እየዘከሩ ለሌላው ታሪክ ፈጽሞ ቦታ ያለመስጠት፣ በመተዋወቅ ላይ የተመሰረተ፣ መከባበር፣ እና tolerance እንዳይኖር ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው። "ከዛፍ ላይ አወረድን" ፣ "ልብስ አለበስን" ፣ "እርሻ አስተማርን" ፣ "አሰለጠንን" ወዘተ የሚሉ የትምክህት ድንቁርናዎች ምንጫቸው የውጪ ethnographers እንኩዋን ሳይቀር የመሰከሩለት፣ የራሱን የመገበያያ ሳንቲም ሳይቀር የቀረጸ፣ በራሱ ንጉስ የሚመራ "advanced" የሆነ ማህበረሰብ kingdom መስርቶ በወላይታ፣ በከምባታ፣ በከፋ ወዘተ ይኖር እንደነበር የሚያሳውቅ የታሪክ ትምህርት ባለመሰጠቱም ጭምር ነው። የ 70 % ኢትዮጵያኖች ቅድመ-ምኒሊክ ታሪክ ፈጽሞ ያልተወሳው የተጻፈ ታሪክ ስለሌላቸው ነው የሚል ሰንካላ ምክንያት ሲሰጥ በብዛት እንሰማለን። ሀቁ ግን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በሙሉ የተጻፈ ታሪክ ባይኖራቸውም ሁሉም የሀገራቸውን ታሪክ በካሪኩለም ቀርጸው ያስተምራሉ። ጽሁፍ አንዱ እንጂ ብቸኛው የታሪክ ምንጭ አይደለም። በብዛት በጽሁፍ ተቀመጠ የሚባለው ታሪክም፣ ድርጊቱ በሚፈጸምበት ቅጽበት የተጻፈ ሳይሆን የተወሰኑ አስርተ (ምናልባትም መቶ) አመታትን በቃል ሲተላለፍ ቆይቶ፣ ከዛ በኋላ በጽሁፍ የሰፈረ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። የመጽሀፍ ቅዱስ አራቱ ወንጌሎች እንኩዋን ክርስቶስ ከሞተ ከተወሰኑ አስርተ አመታት በኋላ የተጻፉ እንደሆኑ ልብ ይሉዋል። ለማንኛውም አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ መከባበር የሰፈነባት፣ የሁሉንም ህዝቦቿ እሴቶች እና የታሪክ ትውስታዎች የምታከብር አገር እንድትሆን መስራት ያስፈልጋል። ለዚ ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኩት የደቡብ ህዝቦችን (ኦሮሚያን ጨምሮ) ታሪኮች በሚገባ በሚዘክር መልኩ የታሪክ ትምህርት ካሪኩለማችን ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ድጋሚ መቀረጽ ይኖርበታል። #the_hegemony_has_to_come_to_an_end

 
 
 

Comments


Post: Blog2_Post

+201140309104

©2019 by KMN Kush Media Network. Proudly created with Wix.com

bottom of page